Rabia

Blogging For Islam

አዒሻ ቢንት አቡበከር አዒሻ (ረ አ)

አዒሻ ቢንት አቡበከር አዒሻ (ረ አ)

 

images (5)

 

አዒሻ ቢንት አቡበከር «በእርግጥ እኔ የምሻው አላህን፣ መልእክተኛውን፣ እንዲሁም ዘውታሪ የሆነውን የመጭውን ህይወት መኖሪያ (ጀነት) ነው።» አዒሻ (ረ አ) የአዒሻ የህይወት ታሪክ ሴት ልጅ እንደ ተቃራኒ ፆታዋ አዋቂና የምሁራን መምህር ለመሆን ብቃት እንዳላት ያረጋግጥልናል። በተጨማሪም ሴት ልጅ በወንዶች አስተሳሰብ ላይ ተፅእኖ በመፍጠር የአመለካክትና የአመራር ምንጭ መሆን እንደምትችል ፥ አልፎ ተርፎም በእንስትነቷ ለባልተቤቷ የደስታና የምቾት ምንጭ ለመሆን ብቃት እንዳላት ግልፅ ማስረጃነት አለው። አዒሻ የአንድም ዩኒቨርስቲ ምሩቅ አልነበረችም። እንዲያውም በዘመኗ ዩኒቨርስቲም አልነበረም። ግና እንደማር ያንቆረቆረቻቸውን ንግግሮቿ በቋንቋ መካነ ጥናቶች እየተጠኑ ነው። ህግን በሚመለከት የተናገረቻቸው በህግ ኮሌጆች ይጠናሉ። እንዲሁም ከህይወት ታሪኳ የሚነበቡ ድርጊቶችዋ የሙስሊሞችን ታሪክ በሚያጠኑ ተማሪዎችና ምሁራን ከሺህ አመታት በላይ እረተዳሰሱ ነው። አዒሻ የእውቀት ባህር ለመሆን የበቃችው ገና በወጣትነት እድሜዋ ነው። ልጅ ሆና ያደገችው በአዋቂነታቸውና በመልካም ስነ ምግባራቸው በሚታወቁት በአባቷ በአቡበከር ቤት ነው። አኢሻ በማራኪው ውበቷና በአስደናቂው የማስታወስ ችሎታዋ የታወቀች ነበረች። በወጣትነት ጊዜዋ የነብዩ የልብ ተፈቃሪና ታሳቢ ለመሆን በቅታለች። በሚስትነትም የቅርብ ወዳጃቸው ለመሆን በመታደሏ ሌሎች ሴቶች ሊያካብቱት ያልቻሉትን እውቀት ከርሳቸው ለማግኘት ችላለች። የነቢዩ ሚስት የሆነችው የ10 አመት ልጅ ሳለች በመካ ሲሆን፥እስከሁለተኛው አመተ ሂጅራና በግምት የ14 ናየ15 አመት ወጣት እስከሆነችበት ጊዜ ድረስ ሰርጓ አልተከናወነም። የሰርጓን ስነ ስርዓት በተመለከተ እንዲህ ስትል ተርካልናለች፦ «አንድ ቀን እየተጫወትኩ ነበር። ረጅሙና ዘንፍላው ፀጉሬ በወጉ አልተጐነጐነም። ቤተሰቦቼ ከምጫወትበት ቦታ መጥተው ወደቤት በመውሰድ ለሰርግ እንድዘጋጅ አደረጉኝ። በባህሬይን የተሰራ ቀይ ሰረዝ ያለው የሙሽራ ልብስ አለበሱኝ ። እናቴም ጥቂት የመዲና ሴቶች ከበር ላይ ቆመው ወደሚጠብቁባት አዲሱ ጐጆዬ ወሰደችኝ። (ጋብቻሽ ለመልካምና ለደስታ ይበለው ሁሉም ያማረ ይሁንልሽ) ስሉም በደስታ ተቀበሉኝ። ከዚያም በፈገግታ የተሞሉት ነቢይ በተገኙበት የዋንጫ ወተት ቀረበ። ነቢዩ (ሰ አ ወ) ከወተቱ ተጐንጭተው ሰጡኝ ። እኔም ስላፈርኩኝ በእጄ እንደያዝኩት ቀረሁ። ቢሆንም እንድጠጣ ስላደፍፈሩኝ ጠጣሁ። ቀሪውን ከ አጠገቤ ተቀምጣ ለነበረችው እህቴ ለአስማ አሳለፍኩ። በዚህ አይነት ሁኔታ ሁሉም እየተቀባበሉ ተጐነጩለት። በዚህ እጅግ ቀላልና የተባረከ በሆነ መልክ ነበር የጋብቻ ስነስር አቱ የተካሄደው።» የነብዩ ሚስት መሆኗ የጨዋታ ህይወቷን አልገታውም። ወጣት ጓደኞቿ ከቤት ሊጐበኟት አዘውትረው ይመጡ ነበር። ስለዚህም ሁኔታ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ «ጓደኞቼ ከሆኑ ልጃገረዶች ጋር በመጫወት ላይ ሳለሁ ነቢዩ በሚገቡበት ጌዚ ጓደኞቼ ቤቱን ለቀው ይወጣሉ። ነቢዪም የእነርሱ ከኔ ጋር መሆን እንደሚያስደስተኝ ስለሚያውቁ ለኔ ውዴታ ሲሉ እንዲመለሱ ያደርጓቸዋል። እንዲያም ሲል በጨዋታቸው ላይ ይሳተፍሉ።» የአዒሻ የመጀመቲያው የመዲና ህይወቷ ትጋትና ጥንካሬን የሚጠይቅ ፈታኝ አጋጣሚ ነበር። በ አንድ ወቅት አባቷና ከርሱ ዘንድ ያረፍ ሁለት አስሃባዎች በመዲና በተወሰኑ ወቅቶች የተለመደ በሆነ አደገኛ ትኩሳት ታመሙ። በዚያን ጊዜ አዒሻ አንድ ጠዋት አባቷን ለመጐብኘት እንደሄደች ሦስቱም በሽተኞች ተዳክመውና ሰውነታቸው ሟሾ ስላገኘቻቸው ከባድ ድንጋጤና ተስፍ የመቁረጥ ስሜት አደረባት። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ አባቷ ምን እንደሚሰማቸው ስትጠይቅ፥ ትርጓሜው ባልገባት የቁርአን ምእራፍ መለሱላት። በሁኔታው እጅግ ተረብሻ ወደቤቷ በመመለስ ለነቢዩ፥ «በሽታው ስለጠናባቸው ይቃዣሉ።» አለቻቸው። ነቢዩም ምን እንዳሉ ጠየቋት። ምንም እንኳ ትርጓሜው ባይገባትም የሰማችውን ንግ ግር ቃል በቃል ነገረቻቸው። ከንግግሯም ነቢዩ የበሽተኞቹን ሁኔታ ለመረዳት ቻሉ። ይህ ገጠመኝ እጅግ አስደናቂ የሆነውን የማስታወስ ችሎታዋን ያሳየናል። ይህም ችሎታዋ ጊዜ እየገፍ በሄድ ቁጥር በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ የነቢዩን ንግግሮች አንድታክማች አግዟታል። ነብዩ በመዲና ሳሉ ከሚስቶቻቸው ሁሉ አዒሻን ይበልጥ ይወዱ እንደነበር ግልፅ ነው። አንዳንዱ ባልደረባዎቻቸው አዘውትረው «የ አላህ ልዑክ ሆይ በዓለም ላይ እጅግ በጣም የሚወዱት ማንን ነው?» ሲሉ ይጠይቋቸው ነበር። ለዚህም ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ እንደ ጥያቄው ባህሪ የሚለያይ ነበር። ለሴት ልጆቻቸውና ለነርሱም ልጆች፥ ሌላ ጊዜ ለ አቡበከር፥ ለዓሊ፣ ለዘይድና ለልጁ ለኡሳም ውዴታ እንዳላቸው አሳውቀዋል። ከነቢዩ ህልፈት በኋላ አዒሻ ለ50 አመታት ያህል ኖራለች። የትዳር ዘመኗ አስር አመታት ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህ ጊዜያቶች አብዛኛውን ያሳለፈችው የአላህ መመሪያ የሆኑትን ሁለት ታላላቅ የእውቀት ምንጮች ቁርአንና ሱናን በማጥናት ነበር። አኢሻ ቁርአንን በልባቸው ከቋጠሩት ሦስት የነቢዩ ሚስቶች አንዷ ነበረች ። ሁለቱ ሀፍሷ እና ኡሙ ሰላማ ነበሩ።ሀፍሷ እና አዒሻ ነብዩ ካለፉ በኋላ የተከተበ የቁርአን ቅጅ ነበራቸው። ዓኢሻ (ረ አ) የጋን መብራት አልነበረችም። እውቀቷን ለሌሎች በማስተላለፍና ማህበራዊ መሻሻሎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክታለች። ብምታስተምርበት ጊዜ ልብን የሚስብና ግልፅ የሆነ የነግግር ለዛ ነበራት። የንግግር ኃይሏ በንፅፅር ሁኔታ አል አህናፍ በተባለ ሰው እንደተከተለው ተገልጿ፦ «የአቡበከርንም ሆነ የኡመርን ንግግሮች አድምጫለሁ። የኡስማንን ፣ የዓሊን ፣ እንዲሁም እስካለሁበት ገዜ ድረስ ያሉ ተተኪዎችን እንደዚሁ። ነገር ግን በእውነቱ ከዓኢሻ አፍ እንደሰማሁት ያለ እጅግ የሚማርክና በጣም የተዋበ ንግግር ከማንም አልሰማሁም።» እውቀት ለመገብየት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ድንበር አቋርጠው ይመጣሉ ። የሴቶቹ ቁጥርም ከወንዶቹ እንደሚበልጥ ይነገራል። ለሚቀርብላት ጥያቄ መልስ ከመስጠቷ በተጨማሪ በጥበቃዋ ስር በርሷ መመሪያ መሰረት የምታስጠናቸው የቲም የሆኑ ልጆችና ልጃገረዶች ነበሯት። እነርሱም ከርሷ መመሪያ ከሚቀበሉት ዘመዶቿ ተጨማሪ ናቸው። ከዚህም የተነሳ ቤቷ ት /ቤት ነበር ለማለት ይቻላል። ዓኢሻና የአላህ ፍራቻዋ መልእክተኛው (ሰ አ ወ ) ለተወዳጇ ሚስታቸው የነበራቸውን ፍቅር የማያውቅ ማን አለ? ከማንም በላይ ማንን እንደሚወዱ ሲጠየቁ ዓኢሻን ብለው መልስ ሰጥተዋል።በኢስላማዊ ህግጋት ከፍተኛ እውቀት የነበራት ከመሆኑ የተነሳ ታላላቅ ሶሀባዎች በዚህ ዘርፍ መፍትሄ ፍለጋ ወደ እሷ ይሄዱ ነበር። ጅብሪል (አሰሰላሙ አለይኩም) በማለት ሰላምታ ያቀርብላት ነበር። መልክተኛውም በአንድ ወቅት በጀነትም ባለቤታቸው እንደምሆን ነግረዋታል። በሙናፍቃን ስትታማ አላህ ከሀሜቱ ነፃ መሆኗን ያረጋገጠላት የቁርአን አንቀጽ በማውረድ ነበር። ኢብን ሰእድ እንደጠቀስነው ዓኢሻ (ረ አ) በአንድ ወቅት አላህ ከሌሎች የመልእክተኛው ሚስቶች በተለየ የሰጣትን አስርያህል ጥሩ ባህሪዋን ቆጥራልች።እነዚህ ባህራዎች ቢኖሯትም አላህን ከመፍራቷ ይተነሳ የሚከተሉትን ስትል ትደመጥ ነበር። «ሁል ጊዜ አላህን በማወደስ እንድጠመድና በፍርዱ ቀንም ነፃ እንድወጣ ዛፍ አርጐ ፈጥሮኝ በነበር!» «ድንጋይ ወይንም አፈር ባደረገኝ!» «ቅጠል ወይንም ሳር ባደረገኝ!» «ባልተፈጠርኩ!» ከታላቋ ኸዲጃና ከፍጢመቱ ዘህራእ(አንፀባራቂዋ) (ረ አ) ቀጥሎ ዓኢሻ በኢስላም ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣት ድንቅ ሴት ናት። በነበራት ጠንካራ ሰብእና በሁሉም መስክ ማለትም በእውቀት፣ በማህበራዊ ኑሮ፣ በፓለቲካና በጦር ሜዳ የመሪነት ስፍራ ይዞ ነበር። ዓኢሻ በዘመኗ ከነበሩ ሴቶች የክብርትነትን ደርጃ ለማግኘትና መልካም አርአያ ለመሆን በቅታለች። በ 58 ኛው ዘመን ሂጅራም በወርሀ ረመዷን ከዚህ አለም በሞት ተሰናበተች። በኑዛዜዋ መሰረት በመዲና በቂእ በተሰኘው የቀብር ስፍራ ከሌሎች የነቢዩ አስሀባዎች ጋር አስክሬኗ አረፈ። እኛንም ኢንሻአላህ ከእሷ ብዙ ትምህርቶችን የምንማር አላህ ያድርገን እላለሁኝ።

1 Star2 Stars3 Stars4 Stars5 Stars (No Ratings Yet)
Loading...

Leave a Reply